የኃይማኖት ግጭት በጎንደር: በልዩነቶች መካረር እና በሰላም ግንባታ ዙሪያ የማኅበረሰቡ ዕይታዎች

ማጠቃለያ

  • የጎንደር ከተማ በሙስሊም እና በኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች መካከል ለምዕተ ዓመታት በቆየው ሰላምና አብሮነት ይታወቃል። ይሁን እንጂ የእነዚህ ኃይማኖቶች ግንኙነት ከቅርብ አሥርት ዓመታት ወዲህ እየሻከረ መጥቷል። ለዚህ ማሳያም በሚያዚያ ወር 2014 በሙስሊም ሐዘንተኞች ላይ በደረሰው ጥቃት እና ይህንን ክስተት ተከትሎ በሌሎች የሃገሪቱ ከተሞች በተፈጠሩት የማኅበረሰብ ግጭቶች እና ሰላማዊ ሰልፎች አጻፋዊ ምላሾች ሲሰጡ ተስተዉሏል::
  • የጥናቱ ተሳታፊዎች ለግንኙነቱ መሻከር የተለያዩ ምክንያቶችን ይጠቅሳሉ። ከነዚህም መካከል በኃይማኖቶች መካከል የሚደረግ ፉክክር (በዋነኛነት በሙስሊሞች እና በክርስቲያኖች መካከል በመሬት እና በአምልኮ ሥፍራዎች ላይ)፣ በኃይማኖት ዉስጥ ያለው መከፋፈል፣ በአብያተ ክርስቲያናት እና በመስጂዶች ውስጥ የሚሰጡ ከፋፋይ ትምህርቶች/ስብከቶች እና የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ይገኙበታል።
  • የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች በሚያዝያ ወር 2014 በተከሰተው ግጭት ተጨባጭ እውነታዎች ላይ አሁንም ልዩነቶች ያሏቸው ይመስላል። የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑ የጥናቱ ተሳታፊዎች በአጠቃላይ ከኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች የጥናቱ ተሳታፊዎች የበለጠ የተጎጂዎችን ቁጥር ሲገልጹ፣ የፒያሳ መስጂድ ሙሉ በሙሉ በእሳት ተቃጥሏልም ይላሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ ገለፃዎች ከኦርቶዶክስ ተሳታፊዎች ገለፃ አንፃር የተለያዩ ሆነው ተገኝተዋል። እነዚህና መሰል ልዩነቶች ግጭቱ የመረጃ ፖለቲካ ላይ ምን ያህል ተፅዕኖዎች እንዳሳደረ ያሳያሉ።
  • የኢትዮጵያ ፖለቲካ በጎንደር ኃይማኖቶች መካከል ያለውን ግንኙነት የጎዳ መሆኑ በተደጋጋሚ የሚነሳ ሐሳብ ነው። ይህም ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት የነበረው የብሔር ተኮር ፌደራሊዝም የብሔር እና የኃይማኖት ልዩነቶችን ማስፋቱ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ግጭቱን ከሙስሊም ኃይማኖት ልዩነት ጋር በማያያዝ ሕዝባዊ ውጥረቱ እንዲጨምር ያደረገው ‘ዋሃቢዝም’ እንደሆነ ሲጠቅሱ፣ ሙስሊሞች በበኩላቸዉ ተጠያቂነቱን እንደ ማኅበረ ቅዱሳን ባሉ የኦርቶዶክስ ማኅበራት ከፋፋይ አስተምህሮ ላይ ያስቀምጣሉ።
  • ምንም እንኳን መንግሥት ግጭቶቹን ለመፍታት የነበረው አስተዋጻኦ ይህን ያህል ጠቃሚ ነበር ተብሎ ባይታሰብም ፣ ጥናቱ በኃይማኖቶች መካከል ያለውን ሰላማዊ ግንኙነት ለመመለስ አራት ጠቃሚ ግኝቶችን አስቀምጧል። በመጀመሪያ፣ ስለወደፊት (ስለነገ) የተለያዩ አመለካከቶች የተንጸባረቁ ቢሆንም፣ የትኛውም ተሳታፊ በኃይማኖቶች መካከል የሚከሰትን ግጭት መደበኛና የተለመደ ነገር ነው ብሎ አልተቀበለውም።  በሁለተኛ ደረጃ መረጃ ሰጪዎች አገር በቀል የግጭት አፈታት ሂደቶችን በማስታወስ በጎንደር ከተማ ተግባራዊ ሊደረጉ እንደሚገባቸው ተስፋ ያደርጋሉ። በሦስተኛ ደረጃ ተሳታፊዎቹ ከመንግሥት ጫና ይልቅ በኃይማኖት አባቶች እና በአገር ሽማግሌዎች የሚመሩ  የኃይማኖት ሰላም ግንባታ  መድረኮች  እውነተኛ መድረኮች ሊሆኑ እንደሚችሉ ያምናሉ። በአራተኛ ደረጃ፣ ግጭት የመከላከል ሥራን በተመለከተ መንግሥት ሚናውን በአጠቃላይ ማሻሻል ይገባዋል።

Find the English version of this publication here

  • Recent Publications

    አዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ የክላስተር አደረጃጀትና የሀብት ክፍፍል ተግዳሮቶች፡ የዘይሴ-ጋሞ እና ቀቤና-ጉራጌ ድንበርአካባቢ ግጭቶች

    ይህ ሪፖርት በደቡብ ኢትዮጵያ ከ2010 ጀምሮ የተተገበረውን የአስተዳደር ክላስተር መልሶ ማዋቀር ተከትሎ፣ በዘይሴ እና በጋሞ እንዲሁም በቀቤና እና በጉራጌ ብሔረሰቦች መካከል በተከሰቱ ውጥረቶች ላይ ያተኩራል።

    MORE »